ኢትዮጵያኒዝም ለፓን አፍሪካኒዝም
- sepastopol
- Sep 19, 2015
- 4 min read

ኢትዮጵያኒዝም የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት
ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ‹‹ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ህዳሴ›› (Pan Africanism and African Rendisance) በሚል አጀንዳ ነበር የተከናወነው፡፡
በመጪው ግንቦት በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው 50ኛ ዓመት የአፍሪካ ኅብረት (የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) የወርቅ ኢዮቤሊዩ በዓል፣ በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረውም በዚሁ አጀንዳ ሥር ሆኖ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም፣ ፓን አፍሪካኒዝንም ለማስፋፋትና ለማጠናከር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም ፓን አፍሪካኒዝም እንደ ጽንሰ ሐሳብ ሲተነተን በመላ ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያን ንቅናቄና ጥምረት መገለጫ ነው፡፡ የጥቁሮች አንድነት የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ዕድገት መሠረት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለዘመናት በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩትንና በዚህም ምክንያት በቅኝ ገዥዎች የጥንት ሥልጣኔያቸው ተስተጓጉሏል የሚል እምነት የነበራቸው የአፍሪካ አባቶች የጀመሩት ይኼው ንቅናቄ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያን አንድ ዓይነት የጭቆናና የቅኝ ግዛት ታሪክ የሚጋሩ ብቻ ሳይሆን፣ የመጪው ጊዜ ዕጣ ፈንታቸውንም አንድ ዓይነት ነው ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም ‹‹በጋራ ራስን መቻል›› (Collective Self-Reliance) ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ አፍሪካዊያን ያሉባቸውን ችግሮቻቸውን ማስወገድ የሚችሉት መከፋፈልንና መለያየትን አጥብበው አንድነት ሲፈጥሩ ብቻ ነው የሚል አንድምታም አለው፡፡ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ይኼው ጽንሰ ሐሳብ፣ በአፍሪካዊያን መካከል የሚቀሰቀሱ የእርስ በርስ ግጭቶችን፣ የአስተዳደር ችግሮችንና የማንነት ቀውሶችን ለመፍታት እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ያለመ ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እ.ኤ.አ 2013 በዚህ ስያሜ እንዲጠራ ሲወስኑ፣ ከኅብረቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ የኢዮቤልዩ በዓል አከባበር ጋር እንዲገጥም የተፈለገ ይመስላል፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም በተለያዩ መንገዶች በመላው ዓለም የተንፀባረቀ አፍሪካዊ የፖለቲካ ንቅናቄ ሲሆን፣ ግንባር ቀደም አቀንቃኞቹም በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችና ሥልጣን ያልነበራቸው ነገር ግን ታዋቂ የነበሩ ጥቁር አፍሪካዊያን ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ስመ ጥሩው ኩዋሜ ንኩሩማህ ከአፍሪካ መሪዎች መካከል ግንባር ቀደም ፓን አፍሪካኒስት የነበሩ ሲሆን፣ ማርከስ ጋርቬይ፣ ጥቁር አሜሪካዊው ማልኮም ኤክስ፣ እንዲሁም ደግሞ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ የንቅናቄው አመንጪዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞቹ አንዲት አፍሪካን የመፍጠር ዓላማ ነበራቸው፡፡ በመላው ዓለም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል፣ ፍትሐዊ ያልሆነው የሀብት ክፍፍል እንዲቀርና አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪነቷ አድጎ በቂ ተፅዕኖ ለማድረግ የምትችልበት ዕድል እንዲፈጠር ያለመ ዓላማ ነበራቸው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና የአፍሪካዊያንን ታሪክ፣ ባህል፣ መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለማጣመር ያለመ በመሆኑ በፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ በፀረ ባርነትና በፀረ ዘረኝነት ላይ የተደረጉ ተጋድሎዎችም የዚሁ አስተሳሰብ ፍሬ ተደርገው ይታያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚቀነቀነው የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እ.ኤ.አ በ1945 በእንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ በተደረገው አምስተኛው የፓን አፍሪካ ጉባዔ ላይ የመነጨ ነው፡፡ በወቅቱ የንቅናቄው አንዱ አባት ተደርጎ ስሙ በግንባር ቀደም የሚነሳው ዱ ቦይስ ዋነኛው ተዋናይ እንደነበርም ይነገራል፡፡ በዚሁ ኮንግረስ ላይ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ተቆርቋሪ አፍሪካዊያን የተሳተፉ ሲሆን፣ ዶ/ር ኩዋሜ ንኩሩማህ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታና ሌሎች ለአፍሪካ ነፃነት ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ የነበሩም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በውጭ የሚኖሩ አፍሪካዊያንና አፍሪካ ውስጥ የነበሩ የነፃነት ትግል መሪዎችንና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አቀንቃኞችን በማገናኘቱም የማንቸስተሩ ጉባዔ ቀዳሚው ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ‹‹ወሬ በቃ…›› አሁን በርካታ ተቆርቋሪ አፍሪካዊያን ምሁራን በፓን አፍሪካኒዝም አስፈላጊነትና አግባብነት ላይ እየተመራመሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም ንቅናቄውን ‹‹አፍሪካዊ ብሔርተኝነት›› ለመፍጠር እንደ አብዮት አድርገው ይመለከቱታል፡፡ አብዮቱን ለማሳካትም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት እየተደረገ ያለውን አንድ የአፍሪካ መንግሥት የመፍጠር እንቅስቃሴ ለማሳካት ትልቅ መሣርያ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በቅርቡ ‹‹Conversing Africa: Politics of Change›› የሚል ሥራቸውን ለንባብ ያቀረቡት ሚኮማ ዋ ንጉግ የተባሉት ጸሐፊ፣ የፓን አፍሪካኒዝምን ፍልስፍና አጀማመርና አመጣጥ በውል ከመረመሩ ምሁራን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ንቅናቄው በአፍሪካ ውስጥ እየታዩ ለሚገኙት ቀውሶች ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከየትኛውም አኅጉር በባሰ ሁኔታ አፍሪካዊያን በዓለም በሚስተዋለው ፍትሐዊ ያልሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ሰለባ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያውም እሳቸው ቀስ በቀስ የሚመጣውን አፍሪካዊ ብሔርተኝነት ሳይሆን፣ በአስቸኳይ በዓለም ዙሪያ መታወጅ ያለበት አፍሪካዊ አብዮት ነው ይሉታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ መሪዎች ከፍተኛ ትኩረት ለተሰጠው ለፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ የምሁሩ አስተዋጽኦ ትልቅ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምሁሩ የንቅናቄው ሁለንተናዊ ገጽታ በጥልቀት ተመርምሮ ግልጽ የሆነ ራዕይና ዓላማ እንዲኖረውም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹Enough talk! Enough running around let us dialogue›› የሚለው ድምዳሜያቸው እንደሚያመላክተው፣ ጸሐፊው አፍሪካዊያን ይህንን ብሔርተኝነት በደማቸው ማስገባት ያለባቸው ዛሬን እያሰቡ ሳይሆን፣ ‹‹ሰብዓዊ ፍጡርነት የተነፈጉበትን ዕለትን›› ነው በማለት፣ ይህንን ዕውን አለማድረግ ግን የአፍሪካን ታሪክ እንደ መካድ ይቆጠራል ይላሉ፡፡ ‹‹ወሬ ይብቃ! ወደ ተግባር›› በሚለው አጽንኦታቸው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማና የፓን አፍሪካን ኮንግረስ የንቅናቄው ተቋማዊ መገለጫዎች ሲሆኑ፣ ኅብረቱ ግን በዋናነት በመንቀሳቀስ ላይ ያለው አኅጉራዊ ተቋም ሆኖ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ 2013 ‹‹ፓን አፍሪካኒዝምና አፍሪካን ሬይነስንስ›› በሚል እንዲሰየም የወሰነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 በአዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ አሰባሳቢነት የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) 50ኛ ዓመቱን የሚያከብረውም በዚሁ ንቅናቄ ፊታውራሪነት ነው፡፡ ኅብረቱ አሁንም በገንዘብ በኩል ከውጭ ጥገኝነት ያልተላቀቀና አንዳንዴም ለአምባገነን መሪዎች ሽፋን መሆኑን፣ ውሳኔዎቹን የማስፈጸም አቅሙ ደካማ ነው ተብሎ የሚወቀስ ቢሆንም፣ የአፍሪካን ድምፅ በዓለም ለማሰማት ከፍተኛ መድረክ እየሆነ መምጣቱ ይነገርለታል፡፡ ከዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ በተነሳባቸው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የክርክር መድረኮች አፍሪካን የሚወክለውን የኅብረቱን ቡድን መርተው የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረጉዋቸው ክርክሮች፣ ምዕራባዊያን አፍሪካን እንዲክሱ በመጠየቅ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ያስወሰኑበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ ‹‹ቃል አቀባይ››፣ ‹‹አፍሪካዊ ተከራካሪ››፣ ‹‹የአፍሪካ ድምፅ››፣ ወዘተ በሚሉ አገላለጾች ሲወደሱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ የወቅቱ ፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊሰኝ የሚችለውን እንቅስቃሴ ያደረጉት ግን በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ብቻም አልነበረም፡፡ ‹‹African Development: Dead Ends, New Beginings›› በሚል ለዶክትሬት ዲግሪያቸው መመረቂያ ጽሑፍ ባቀረቡት ሐሳብም፣ አፍሪካ ከምዕራባዊያን ጥገኝነት እንድትላቀቅና የራሷ ነፃ የሆነ አኅጉራዊ ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንድትከተል ተሟግተው ነበር፡፡ በጽሑፋቸውም ከዚሁ የፓን አፍሪካኒዝም ጋር አብሮ እየተነሳ ያለውን ‹‹አፍሪካን ሬይነስንስ›› ጽንሰ ሐሳብም ደጋግመው አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የሚነሳውን ‹‹ህዳሴ›› በአኅጉር ደረጃም ተግባራዊ የማድረግ ህልም የነበራቸው ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያኒዝም ለፓን አፍሪካኒዝም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹የአፍሪካ ድምፅ›› እስከመባል የሚያደርስ አኅጉራዊ ንቅናቄ ቢያደርጉም በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ አይደሉም፡፡ ጥረታቸውም የደርግን ውድቀት ተከትሎ አዲሱ የኢሕአዴግ መንግሥት ገና ባልተደላደለበት ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ለመውሰድ የተደረገውን ሴራ በማክሸፍ ነው የሚጀምረው፡፡ በአገራቸው ፀረ ሕዝብ ነበሩ ያሉዋቸውን አፄ ኃይለ ሥላሴና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአፍሪካ ነፃነት ተጋድሎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንና መስዋዕትነት መክፈላቸውን በማስታወስ ነበር የተከራከሩት፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በተለያዩ የዓላማችን ክፍሎች የተካሄዱት የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄዎች ‹‹ኢትዮጵያኒዝም››ን እንደ መሠረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ራሳቸውን ‹‹አፍሪካዊ ኢትዮጵያ›› እያሉ የሚጠሩ ናቸው፡፡ ከሳምንት በፊት ከተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ቀደም ብሎ ‹‹በፓን አፍሪካኒዝም›› ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሒልተን ሆቴል በተካሄደ ውይይት ላይ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በነጮች ላይ ያካሄዱት ተጋድሎና በተለይ ደግሞ በዓድዋ ጦርነት በአውሮፓዊ ወራሪ ኃይል ላይ በተገኘው ድል ምክንያት፣ በተለያዩ የዓለም አቅጣጫዎች የተለኮሱ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄዎች መሠረታቸው በሙሉ ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› ነበር ብለዋል፡፡ ከፓን አፍሪካኒዝም በፊትም ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሱ አቀንቃኞች በዓለም ዙሪያ እንደነበሩም አውስተዋል፡፡ ኢትዮጵያኒዝም የፓን አፍሪካኒዝም ምንጭ መሆኑን ባደረጉት ገለጻ አስረድተዋል፡፡ አሁንም ንቅናቄው ከአፍሪካ ህዳሴ ጋር ትስስር እንዲኖረው የተደረገውን ጥረት አድንቀው፣ ‹‹አፍሪካዊያን የሚጋሩዋቸውን የጋራ እሴቶች፣ ቁርጠኝነትና ተስፋ ተጠቅመው ያሉባቸውን የጋራ ችግሮች ማስወገድ አለባቸው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያዊነትና በፓን አፍሪካኒዝም መካከል ያለው ትስስር ግን የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Comments