top of page
Search

ኢህአዴግ በመንግሥት በጀት ለካድሬዎችና አባላቱ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

  • Writer: sepastopol
    sepastopol
  • Mar 16, 2015
  • 1 min read

siye01.jpg

መጋቢት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ ካድሬዎችን የሚያሰለጥነው አካዳሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በመለስ ዜናዊ ስም የተሰየመው የአመራር አካዳሚ በመንግስት በጀት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአምስት ዙሮች 2ሺ 500 ያህል ከፍተኛ አመራሮችን፣ ከ30ሺ በላይ መካከለኛ አመራሮችን አሰልጥኗል፡፡

አካዳሚው ያለአንዳች ፈቃድ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ሲሰራ ከቆየ በሃላ በ2006 ዓ.ም በሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 321/2006 ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠ/ሚኒስትሩ በማድረግ መንግሥታዊ ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል፡፡

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በሱሉልታ አካባቢ በ50ሺ ካሬሜትር ቦታ ላይ ዋና የማስልጠኛ ተቋሙን እየገነባ ሲሆን እስካሁን ከየመንግስት መ/ቤት የሚመረጡ ካድሬዎችን ለማሰልጠን በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩት የመንግሥትና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለለስልጣናት እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው በሥራ አመራር ዕውቀት በቂ ሥልጠናና ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች የሌሉት ሲሆን፣ ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በአመዛኙ አመራር ብለው የሚሰጡት ስልጠና በኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ላይ ብቻ ያተኮረና ሳይንሳዊ የአመራር ክህሎት ሥልጠናን ያላቀፈ ነው ብለዋል፡፡

ሥልጠና የወሰዱት አመራሮች ወደሲቪል ሰርቪስ መ/ቤቶች ሲመለሱ ሠራተኛውን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት፣ በለውጥ ሠራዊት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲሰሩ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም መንግሥታዊ ተቋማትና እንጀራ ፈላጊው ሰፊው ሠራተኛ የአንድ ፓርቲ መገልገያ እንዲሆኑ እየተገደዱ መሆኑን ያሳያል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።

በተጨማሪም ኢህአዴግ በመንግስታዊ አደረጃጀትና በመንግስትና በህዝብ በጀት የራሱን አባላትና ካድሬዎች በዚህ መልኩ ማሰልጠኑ ሕገወጥነት መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ በመንግስት ወጪ በመላ አገሪቱ ለተሰማሩ የሚሊሺያ አባላት ስልጠና እየሰጠ ነው።

ሚሊሺያዎቹ በደህንነት መስሪያ ቤት በተቀረፀው የገጠር ሚሊሻዎች የምርጫ አፈፃፀም መመሪያ እየሰለጠኑ ሲሆን፣ መራጮች ኢህአዴግን እንዲመርጡ ለማስገደድ ሚሊሺዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጡዋቸዋል።

ሚሊሺዎች በአንድ ለአምስት በተቀመጠው አደረጃጃት መሰረት መራጮችን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመውሰድ ለኢህአዴግ ድምጽ መስጠታቸውን ያረጋግጣሉ። በኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ላይ ከማስፈራራት ጀምሮ ድብደባ እስከመፈጸም፣ ይህም ሆኖ ካልተገኘ ስውር በሆነ መንገድ ስለሚወስዱት ጥብቅ እርምጃ ስልጠና ይወስዳሉ።

በአንዳንድ ክልሎች ሚሊሺዎች ቀደም ብሎ ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች ደግሞ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ስልጠናው ተጠናክሮ እየተሰጠ ነው።

 
 
 

Comments


    ሰባስቶፖል የመይሳው 
ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት !

ጋዜጠኞች ይፈቱ 

ጦማርያኑ ይፈቱ 

ፖለቲከኞች ይፈቱ 

ወያኔ ይውረድ 

ብሔራዊ ውርደት በቃ 

   አንድነት ለነጻነት  
  ይከታተሉን 
  • Facebook Basic Black
  • Twitter Basic Black
  • Google+ Basic Black

ተዛማጅ ገጾች 

news
news
g7pf news
arbegnoch

         ያነበቡትን ወደዉታል ? አንግዲያውስ ላንባቢዎች አዳዲስ መረጃዎችን ለማቅረብ ይተባበሩን ..ኢትዮጵያኒዝም 

Donate with PayPal

© 2023 by "This Just In". Proudly created with Wix.com

bottom of page