top of page
Search

የእንግሊዝ የፓርላማ አባላት በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ለመደራደር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ

  • Writer: sepastopol
    sepastopol
  • Jan 17, 2015
  • 1 min read

አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ወር ከባለቤታቸው ጋር በስልክ ተነጋግረዋል

የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን የያዘ የልኡካን ቡድን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ማስፈታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር በቀጣዩ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ትናንት ዘገበ፡፡ ሁሉንም የእንግሊዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት የያዘው የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ጀርሚ ኮርባይን የሚመሩት የልኡካን ቡድኑ፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመምከር የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንዳይሆንና ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው እንደመሆኑ የእንግሊዝ መንግስት ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥቶ መከታተልና ግለሰቡን ከሞት ማዳን ይጠበቅበታል ያሉት ኮርባይን፤ ቡድኑ አቶ አንዳርጋቸው ግልጽ ባልሆነና ተቀባይነት በሌለው የህግ አካሄድ ለእስር ተዳርገዋል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አቶ እንዳርጋቸው የአሸባሪ ቡድን አባል ቢሆኑም በእስር ላይ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ነሃሴና ታህሳስ ወር ላይ ከተደረጉት ሁለት የመንግስት ተወካዮች ጉብኝቶች ውጭ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጎብኘት እንዳንችል አግዶናል ብለዋል፡፡ የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ በግለሰቡ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደቀጠለበትም አስረድተዋል፡፡በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢትዮጵያን መንግስት ለማፍረስ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን አባል ናቸው፣ በእስር ላይ ሆነውም ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤ እስረኞችን ማሰቃየት ኢሰብአዊ ድርጊት እንደመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ አይደለም ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸምባቸው ስቃይ እያየለ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ባለፈው ወር እንግሊዝ አገር ወደምትገኘው ባለቤታቸው ስልክ ደውለው መገናኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአብዛኛው ስለልጆቻቸው ጉዳይ እንዳወሩ፣ ደህንነታቸውን እንደገለጹላቸው፣ እንዲሁም ለልጆቼ የማይሆን ተስፋ መስጠት አልፈልግም ማለታቸውን ባለቤታቸው እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡

 
 
 

Comments


    ሰባስቶፖል የመይሳው 
ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት !

ጋዜጠኞች ይፈቱ 

ጦማርያኑ ይፈቱ 

ፖለቲከኞች ይፈቱ 

ወያኔ ይውረድ 

ብሔራዊ ውርደት በቃ 

   አንድነት ለነጻነት  
  ይከታተሉን 
  • Facebook Basic Black
  • Twitter Basic Black
  • Google+ Basic Black

ተዛማጅ ገጾች 

news
news
g7pf news
arbegnoch

         ያነበቡትን ወደዉታል ? አንግዲያውስ ላንባቢዎች አዳዲስ መረጃዎችን ለማቅረብ ይተባበሩን ..ኢትዮጵያኒዝም 

Donate with PayPal

© 2023 by "This Just In". Proudly created with Wix.com

bottom of page